መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ተቋማት ጋር የቴክኖሎጅ ሳምንት አካሄደ፡፡

Info Latest News

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስተሪ ግንኙነት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዘመኑ ከደረሰበት የፈጠራና ቴክኖሎጅ ውጤቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና በዩኒቨርሲቲው ከባቢ የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች በማሰባሰብ በዩኒቨርሲቲው ስቲም ሴንተር እንድካተቱ በማድርግ ፈጠራቸውን በማስፋት ሌሎች እንዲጠቀሙበት የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ስር ከሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ተቋማት የተውጣጡ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ያላቸውን ቴክኒክና ሙያ ተቋማት በዩኒቨርሲቲው በመገኘት የፈጠራ ውጤታቸውን ከግንቦት 28-29/2013 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፣የፈጠራ ባለቤቶችና የኮሌጆቹ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ስራቸውን እንድያሳዩ እድል ተፈጥሯል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ካሳሁን አህመድ የቴክኖሎጂ ሳምንቱን መከበር ባበሰሩበት ወቅት እንደተናገሩት በዞናችን ያሉት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና የቴክኒክ ሙያ ኮሌጆች ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ውጤቶችን በማበረታታት ወደ ማህበረሰቡ ደርሰው አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ዩኒቨርሲቲው ከጎን ሆኖ የመደገፍና እውቅና የመስጠት ስራ ለመስራት የቴክኖሎጂ ሳምንት ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ስለሆነ ነው ሲሉ ተናግረው በየተቋሙ የተመረጡ ፈጠራዎችን በማባዛት ለስራ አጥ ወጣቶች ተደራሽ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስተሪ ግንኙነት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር መምህር ዳዊት ዲበኩሉ በበኩላቸው የቴክኖሎጂ ሳምንት ያስፈለገበት ምክንያት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በፈጠራ ስራ እንዲበረታቱ ለማድረግና የሰሩትን ስራ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ይሆን ዘንድ ለማስተዋወቅ እንደሆነ አክለው ገለፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.