“ሳይማር አስተማረን” ለምንለው ወገናችን አገልግሎታችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን መሆን ይገባዋል!

Latest News

አገራት የሃብት መጠናቸው የቱንም ያህል ቢሆን ዜጎቻቸው የዘመናዊ ትምህርት እንዲቀስሙላቸው የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ዓለም በአዳዲስ ፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ በገባችበት በዚህ ጊዜ ጭራ ሆኖ ከመከተል ወጥቶ መሪ ለመሆን በማለም አገራት መዋዕለ ንዋያቸውን ትምህርት ላይ ያፈስሳሉ፡፡ 

የአገራችንን ፅኑ ፍላጎት ስናይ በ2012 በጀት ዓመት መንግስት እንደሀገር ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍንና ለዘላቂ ግቦች ማሳኪያ የተፈቀደውን ጨምሮ 386.9 ቢሊየን ብር ገደማ መድቦ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ (ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ለተጠሪ ተቋማትና ለ45ቱ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) የተመደበው 48.4 ቢሊየን ብር ሲሆን ከአጠቃላይ የፌደራል በጀት የ20.15% ድርሻን ይይዛል፡፡ ይህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡ 

“ለትምህርትና ስልጠና ብቻ ለምን ይህን ያህል ወጪ ይወጣል” ካልን ትምህርት ለአገር ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ስለሆነ ነው፡፡ ትምህርት ለሰብአዊ እድገት ፣ ለኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ፣ ለማህበራዊ ደህንነት ፣ ለግላዊ እርካታ እና ዘላቂ የሆነ ፕላኔት እንዲኖር ለማድረግ መሠረት ነው፡፡ 

መማር አዲስ መረዳትን ፣ ዕውቀትን ፣ ባህሪያትን ፣ ክህሎቶችን ፣ እሴቶችን ፣ እና ምርጫዎችን የማግኘት ሂደት ነው። መማር የአእምሮን አስተሰሳብ ለማስፋት ያግዛል፡፡ ትምህርት የህይወት ተሞክሮ ለማግኘት ይረዳል ፡፡ መማር ብዙ ክህሎቶችን ቀስመን በተግባር የተሻልን ሆነን እንድንወጣ ያመቻቻል፡፡

ታዲያ ብዙ የአገር መዋዕለ ንዋይ ፈስሶለት የተማረው ዜጋም ኮቪድ 19ን ለመዋጋት ከኛ ምን ይጠበቃል?
“ሳይማር አስተማረን ህብረተሰብ ማገልገል እፈልጋለሁ” የሚል ፍላጎት ከሁሉም ወገን ይሰማል፡፡ እርግጥ ነው ያንን የምናሳይትጊዜ ላይ ነን! “ሳይማር አስተማረን የምንለውን ህብረተሰብ” የምናገለግልበት ትክክለኛ ጊዜ ዛሬ እና አሁን ነው!
መማር የባህሪ ለውጥ ለማምጣትና አዳዲስ እውቀቶችን ይዞ ለመተግበርም ያግዛልና በመጀመሪያ የኮቪድ 19ን ስርጭት ለመከላከል መተግበር ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ሁሉ እንደ ግለሰብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 
ከዚያ ራሳችን እየተጠነቀቅን ከወንድም እህቶቻችን፣ ቤተሰቦቻችን ጎረቤቶቻችን ጀምረን በአከባቢያችን ላሉት ወገኖቻችን ሁሉ የቫይረሱን አደገኛነትና የመዛመቻ መንገዶቹን በማስተማር፣ የጥንቃቄ መንገዶችን ሁሉ እንዲተገብሩ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ቫይረሱን አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ በማገዝ፣ በጥንቃቄ መጠናችን ለሌሎች አርአያ ሆነን ወገኖቻችንን ልናነቃ ይገባል፡፡ 
የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ማህበረሰቡ ቁጥር ከፍተኛ እንደመሆኑ ራሳችን እየተጠነቀቅን ሌሎች እንዲጠነቀቁ በተለያዩ መንገዶች ማስተማር ከቻልን የምናተርፈው ህይወት ብዙ ነው፡፡ 
በተለይ ወገኖቻችን “እኔ ጋር አይደርስም” ከሚል አስተሳሰብ እንዲወጡ፣ በይሉኝታ ተይዘው ከቀጠሉት ማህበራዊ መስተጋብር ተላቅቀው አካላዊ እርቀታቸውን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
በጋራ ሆነን ስንጠነቀቅ፣ ወገኖቻችንን ተባብረን ስናነቃ ቫይረሱ የሚያደርስብንን ሁለተናዊ ጉዳት በእጅጉ መቀነስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ራሳችን ቀድመን ነቅተን “ሳይማር አስተማረን የምንለውን ህብረተሰብ” አንቅተን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ድል ለማድረግ ዛሬ፣ አሁን፣ እንነሳ! አንዘናጋ!

ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር  ፌስቡክ ፔጅ ላይ የተወሰደ

Leave a Reply

Your email address will not be published.