በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ቅርስና ሀገር በቀል እውቀቶች አስተባባሪነት የዩኒቨርሲቲውን ልዑካን በማዋቀር እና ሌሎች ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ከደቡብ ወሎ ዞን ባህል ናቱሪዝም መምሪያ እንድሁም ታሪካዊ ቦታው የሚገኝበት የተንታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝምና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች በተገኙበት የአጼ ቴዎድሮስን 154ኛ ዓመት የዝክረ ሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን በማስመልከት ‹‹ያለንን እንወቅ፣ ያወቅነውን እናሳውቅ አኩሪ ታሪካችንን እንዘክር›› በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 9/2014 ዓ.ም የጉብኝትና የትውወቅ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡በመርሀ ግብሩም በአንድ ወቅት የአጼ ቴወድሮስ መናገሻ ስለነበረችው ስለ መቅደላ አምባ፣ በውስጧ ስለሚገኙ ልዩ ልዩ ታሪካዊ ስፍራዎች በተንታ ወረዳ ባህል ና ቱሪዝም ባለሙያ ፣በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር፣ ከክልልና ከዞን በመጡ የባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎች ስለታሪካዊ ቦታው ምንነት በዝርዝር ገለፃ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ ቦታው ታሪካዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለማልማት ምን መደረግ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም / ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮነን በቦታው ተገኝተው እንደተናገሩትም ታሪካዊ ስፍራው የሀገራችን ትልቅ የታሪክ አካል በመሆኑ መገፋፋት ሳይኖር የደበዘዘውን አሻራ ጨርሶ ሣይጠፋ ታሪካዊ ይዘቱን እንደጠበቀ የማልማት ሃላፊነት የሁሉም መሆኑን አስታውሰው መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲም የቦታውን ስያሜ ወስዶ ከመጠቀሙ በሻገር ቦታን በተደራጀ መልኩ የማልማትና የመጠበቅ ሀላፊነት አለበት ብለዋል ፡፡የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ መካነሰላም ካምፓስ ኤክስኩዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ አብዱረህማን አወል ዩኒቨርሲውን ወክለው ንግግር ባደረጉት ወቅት እንዳሉትም ታሪካዊ ቦታውን የሚገባውን እንክብካቤ ለማድረግና ለማልማት በኒቨርሲቲው በኩል ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል፡፡የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ቅርስና ሀገር በቀል እውቀቶች አስተባባሪ የሆኑት መምህር አብርሀም በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት ጉብኝቱ የተዘጋጀበት አላማ ታሪካዊ ቦታውን የማስተዋወቅ፣ለጥናትና ምርምር መነሻ ሀሳብ ለመያዝ እና ለአካባቢው መነቃቃትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸው ታሪካዊ ቦታው ከክልሉ ጀምሮ ሁሉም የሚመለከተው አካል በጋራ መስራት ቢችል ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር ትልቅ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችል ቦታ ነው ብለዋል፡፡ መቅደላ አምባ ከደሴ 157 ኪሎ ሜትር ፣መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ቱሉ አውልያ ከተማ 69 ኪሎ ሜትር ፣ከተንታ ወረዳ አጅባር ከተማ 29 ኪሎ ሜትር ርቀት ልዩ ስሙ 019 ደበቅ እየተባለ በሚጠራው ቀበሌ የሚገኝ ታሪካዊና ስትራቴጅካዊ አምባ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ለታሪክ መዘክርነት የሚገኙት 16 ሽህ ፓውንድ የሚመዝነው ሴቫስቶፖል የተባለው ትልቁ መድፍ ፣ ከ2-3 ሺ ኪሎ ግራም የሚመዝነው የአጼ ቴዎድሮስ ትንሽ መድፍ ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የቦይ ምሽግ ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የውኃ ግድብ ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ጊዜያዊ ቤተ-መንግስት ፣ ዕቃ ግምጃ ቤት ፣የፊታውራሪ ገብርየ አዳራሽና የመቅደላ መድኃኒያዓለም ቤተ-ክርስቲያን ፍርስራሽ ፣ የአጼ ቴዎድሮስ መካነ መቃብርና አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በክብር የሰውበት ቦታ ናቸው፡፡አምባው 4 ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሆኖ ርዝመቱ 2.5 ኪሎ ሜትር ወርዱ 1.5 ኪሎ ሜትርና ከፍታው 2787 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ነው፡፡
210You and 209 others4 Comments17 SharesLikeCommentShare