የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ አካሄደ።

Research News University News

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ አካሄደ።

(ግንቦት 19/2024 የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት)

በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጅ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት አዘጋጅነት ” Holistic Research: Fostering Synergy across Fields”በሚል ተመራማሪዎችን በመጋበዝ ለሁለተኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ አካሂዷል::

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ም/ፐሬዝዳንት ሰዋአገኝ አስራት (ዶክተር) ለተጋባዥ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጅ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ስለሺ አቢ (ዶክተር) ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበት አካባቢ ዩኒቨርሲቲው ስያሜውን ያገኘበት አጼ ቴወድሮስ በክብር የተሰውበት ታሪካዊ የመቅደላ አምባ ተራራና ቦረና ሳይንት ወረሂመኖ ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ታሪካዊ ቦታዎች በዙሪያው የሚገኙበት እንድሁም መልማት የሚችሉ በርካታ ፀጋዎች ያሉት አካባቢ በመሆኑ በምርምር የታገዘ ውጤታማ ስራ መሰራት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳና ቁልፍ ንግግር አቅራቢ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል ስሜነህ ደሴ (ዶክተር) ምሁራን አለምን እየተፈታተኑ የሚገኙ ችግሮችን ለመቅረፍ በምርምር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው ቁልፍ ንግግር ያደረጉት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ አሰፋ ባልቻ (ዶክተር) መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ታሪካዊ ሁነቶች በተፈጸመበት አካባቢ የተመሠረተ በመኾኑ እነዚህን ሁነቶች በጥናት እና ምርምር በመደገፍ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መሥራት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቆየው በዚህ የምርምር ጉባኤ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ የምርምር ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው በተግባር እያከናወናቸው የሚገኙ የምርምር ስራዎችን የመስክ ምልከታ የተካሄ ሲሆን በተመለከቱት ስራ መደሰታቸውን የገለፁት ተመራማሪዎች በቀጣይ መሰራት አለባቸው ያሏቸውንም ጉዳዮች ጠቁመዋል፡፡

የአካዳሚክ፣ምርምር፣ቴክኖሎጅ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ስለሺ አቢ (ዶክተር) ባደረጉት የማጠቃለያ ንግግር የዩኒቨርሲቲውን ጥሪ ተቀብለው ለመጡ እንግዶች ያቀረቡት ምርምር ትምህርት የተወሰደበትና ሙያዊ ልምድ የተገኘበት መሆኑን እና ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚሰራቸው ስራዎች ለሰጡት ምክረ ሃሳብ ምስጋና አቅርበው አጋርነታችንንም አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *