መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት (ነሀሴ 18/2018አ.ም ጊምባ/ኢትዮጵያ)
በ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ወቅት የታዩ እጥረቶችን በማረምና የተገኙ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በ2019 ዓ.ም የታቀዱ ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾችን (KPIs) በትጋት በመፈፀም የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ካሳ ሻውል ገለፁ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ነው።
ዶ/ር ካሳ አክለውም በበጀት ዓመቱ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም በአስተዳደርና በልማት ዘርፎች የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራትና ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።
በመድረኩም የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች የቀረቡ ሲሆን ዶ/ር ስለሺ አቢ(የአካ/ም/ማ/ቴ/ሽ/ም/ል ፕሬዝዳንት)፣ ዶ/ር ሰውአገኝ አስራት(የአስ/ል/ም/ል ፕሬዝዳንት)፣ አቶ መላኩ ጌታሁን( የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ተወካይ) እንዲሁም መ/ር ብሩክ ወንደ ( የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ንግድና ማማከር ስራዎች ኢንተርፕራይዝ ስራ አስኪያጅ) የየዘርፋቸውን ሪፖርት በማቅረብ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በመጨረሻም ከግምገማው ማጠቃለያ በመነሳት በ2019 ዓ.ም የእቅድ ትግበራ ወቅት በዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮችና ቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች ላይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና አጋር አካላት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የላቀ ውጤት እንዲመዘግብ የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት ተላልፏል።







